ዐውደ ቢዝነስ
ዐውደ ቢዝነስ
በኢትዮጵያ ከፍተኛ መጠን ያለው የነዳጅ ክምችት መኖሩ በዓለማቀፍ ደረጃ ተረጋገጠ፡፡ በቅርቡ በአንድ የአሜሪካን ድርጅት የተካሄደ ጥናት 7 ትሪሊዮን ኪዪቢክ ጫማ የተፈጥሮ ጋዝ ክምችት መኖሩን አብስሯል፡፡ በቆይታችን ሙሉ መረጃውን ትሰሙታላችሁ፡፡
የቻይናው ግዙፍ የሞባይል ካምፓኒ ሁዋዌ ለኢትዮጵያውያን ስራ ፈላጊዎች አዲስ ዕድል ይዞ መጣ፡፡ዝርዝር አለን፡፡
የኢታኖል ቤንዚን ድብልቅ አቅርቦትን ማስቀጠል ቢቻል ኖሮ ከየወሩ የነዳጅ ግዥ ግማሽ ሚሊዮን ዶላር ማዳን ያስችላል ነበር ተባለ፡፡ ለዚህ ስራ ሲባል የተመሰረተው መስሪያቤት የገባበት ሳይታወቅ ደብዛው ጠፍቶ መቅረቱ ተጠቁሟል፡፡ ሰፊ ዳሰሳ እናደርግበታለን፡፡
የኬኒያ አየር መንገድ ኢትዮጵያ ገንዘቤን ትክፈለኝ ሲል ጥያቄ አቀረበ፡፡ አየር መንገዱ ያቀረበው የገንዘብ ጥያቄ በርካታ ሚሊዮን ዶላሮች መሆኑ ተጠቁሟል፡፡ ዘገባችን በዚህ ላይ ዝርዝር መረጃ ሸክፏል፡፡
የብረትና የሲሚንቶ ምርቶች ከፍ ላለ የገበያ ውስጥ ህገወጥ ድርጊት መጋለጣቸው የኮንስትራክሽን ላይ የተሰማሩ ድርጅቶችን ከጨዋታ ውጪ አድርጓቸዋል ተባለ፡፡ የአንድ ኩንታል ሲሚንቶ ዋጋ በአሁኑ ወቅት 1800 ብር ደርሷል፡፡ በተመሳሳይ ከዓመታት በፊት በ25 ብር ይሸጥ የነበረ ብረት አሁን ላይ ዋጋው 122 ብር መድረሱ ከቁጥጥር ውጪ የወጣው ህገወጥ ገበያ ማሳያ ሆኖ ተጠቅሷል፡፡ ርዕሰ ጉዳዩን በስፋት እንቃኘዋለን፡፡
ዘጠኝ ሚሊዮን ህዝብ ብቻ የሚኖርባት አነስተኛዋ ኢሲያዊት አገር የዘይት ሚንስትር ሾመች፡፡ አገሪቱ በተመሳሳይ የቡና ሚንስትር መሾሟም ዓለምን ጉድ አሰኝቷል፡፡ ይህ አስገራሚ መረጃ በዘገባችን ተካቷል፡፡
////////////////////////////
የተወደዳችሁ የቻናላችን ቤተሰቦችበያላችሁበት ሰላም፤ ጤናና ፍቅር ይበዛላችሁ ዘንድ ልባዊ ምኞታችን ነው፡፡ እነሆ ዐውደ ቢዝነስ ልዩ የፋይናንስ፤ የቢዝነስና ኢኮኖሚ ዘገባ መሰናዷችን ጀመረ፡፡ ከኤርሚ ዘ ኢትዮጵያ የዩቲዩብ ቻናል፡፡
አብራችሁን በመቆየት ለቢዝነስና ስኬት ጥያቄያችሁ ምላሽ የሚሰጡ ወቅታዊ ዘገባዎችን ትካፈሉን ዘንድ በአክብሮት ጋብዘናል፡፡ ሰናይ ቆይታ፡፡
///////////////
የቻይናው ግዙፍ የሞባይል ካምፓኒ ሁዋዌ ለኢትዮጵያውያን ስራ ፈላጊዎች አዲስ ዕድል ይዞ መጣ፡፡ ሁዋዌ በባህርዳር ከተማ ስራ ፈላጊዎችን በአንድ አሰባስቦ አቅምና ችሎታቸውን የመፈትሸ ስራ ማከናወኑ ተዘግቧል፡፡
በዚህ የስራ አፈላላጊ ኩነት ላይ በዘንድሮው ዓመት ከባህርዳር፤ ጎንደር፤ አኒባራና ደባርቅ ዩኒቨርስቲ የተመረቁ ተማሪዎች ተሳታፊ ሆነዋል፡፡ በተጨማሪም የሁዋዌ አይ ሲቲ አካዳሚ ከተለያዩ የአገሪቱ የቴክኒካልና ቮኬሽናል ኮሌጆች በተመሳሳይ ሙያ የተመረቁ አዳዲስ ስራ ፈላጊዎች መረጃን ማሰባሰቡ ታውቋል፡፡
ሁዋዌ በዚህ መድረክ በአጠቃላይ የ800 ምሩቃን የስራ ማመልከቻ ቅፅ ተቀብያለሁ ብሏል፡፡ ከእነዚህ አመልካቾች መካከል ዕድለኛ ሆነው ለተመረጡ 300 ስራ ፈላጊዎች ድርጅቱ የስራ ዕድል እንደሚሰጥ ተናግሯል፡፡
ሁዋዌ እንዲህ አይነት የስራ ዕድል ማስገኛ መደረክ ሲያዘጋጅ የአሁኑ ሁለተኛው ሲሆን፤ ከሦስት ወራት በፊት ከአዲስ አበባ ዩኒቨርስቲ ጋር በመተባበር ተመሳሳይ መድረክ አዘጋጅቶ እንደነበር ለማወቅ ተችሏል፡፡ ሁዋዌ በኢትዮጵያ ውስጥ በአይ ሲቲ ቴክኖሎጂ ግንባታ ተግባር ከተሰማራ ከሃያ ዓመት በላይ ማስቆጠሩ ይታወቃል፡፡
/////////
በኢትዮጵያ ከፍተኛ መጠን ያለው የነዳጅ ክምችት መኖሩ በዓለማቀፍ ደረጃ ተረጋገጠ፡፡ በቅርቡ በአንድ የአሜሪካን ድርጅት የተካሄደ ጥናት 7 ትሪሊዮን ኪዪቢክ ጫማ የተፈጥሮ ጋዝ ክምችት መኖሩን አብስሯል፡፡
ይህ ዓለም አቀፍ ጥናቱ የኢትዮጵያን የመደራደር አቅም ያሳድገዋል ተብሏል፡፡ በቆይታችን ሙሉ መረጃውን እናጋርችኋለን፡፡
ይፋ የተደረገው ይህ ጥናት በኢትዮጵያ በኦጋዴን አካባቢ 7 ትሪሊዮን ኪዪቢክ ጫማ (200 ቢሊየን ሜትር ኪዩብ ገደማ) የተፈጥሮ ጋዝ ክምችት መኖሩ አረጋግጧል፡፡
የማዕድን ሚንስቴር ከአሜሪካው ኔዘርላንድ ስዌል ኤንድ አሶሲሼየትስ ኢንክ ኩባንያ (ኤልሲኤአይ) የጥናት ተቋም ጋር በመተባበር ያስጠናውን የነዳጅ ክምችት ጥናት ይፋ በተደረገበት መርሀ ግብር ላይ እንደተጠቀሰው ኢትዮጵያ በኦጋዴን ተፋሰስ 7 ትሪሊየን ጫማ ጥልቀት ያለው የተፈጥሮ ጋዝ ክምችት እንዳላት ተረጋግጧል ተብሏል።
የማዕድን ሚኒስትሩ ታከለ ኡማ ( ኢ/ር) በመድረኩ ላይ እንዳሉት ጥናቱ ኢትዮጵያ ከዓለም አቀፍ ተቋማት ጋር ያላትን የመደራደር አቅም ያሳድገዋል።
“ከዚህ ቀደም የነበሩ ኩባንዎች ምን ያህል ክምችት እንዳለን አይነግሩንም ነበር” ያሉት ሚኒስትሩ አሁን የተጠናው ጥናት ግን ለክምችቱ መጠን ዓለም አቀፍ ማረጋገጫ መስጠቱን ገልጸዋል፡፡
እንዲሁም የነዳጅ ሀብት መጠናችን በዚህ ጥናት መረጋገጡ በተስፋ ብቻ ሲነገረን የነበረው ነገር ወደ እውነትነት እንዲቀየር ያደርጋልም ሲሉ ሚንስትሩ አክለዋል።
ይህ የነዳጅ ሀብት የአዋጭነት ጥናት ለአራት ወራት የተካሄደ ሲሆን ጥናቱ ኢትዮጵያ በተለምዶ ከሚባለው በትክክል ያላት የተፈጥሮ ነዳጅ መጠን ምን ያህል እንደሆነ የሚያሳይ እንደሆነም በጥናቱ ርክክብ ወቅት ተገልጿል።
የጥናቱን ውጤት ይፋ በማድረጉ እና የብቃት ማረጋገጫ ማስረጃ ርክክብ ሥነ-ሥርዓቱ ላይ የተሉያዩ ተቋማት ሚኒስትሮችን ጨምሮ የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር እና የአሜሪካ ኤምባሲ ተወካዮችም ተገኝተዋል።
ኢትዮጵያ በ2010 ሰኔ ወር ላይ በቀን እስከ 450 በርሜል ድፍድፍ ነዳጅ የማምረት ሙከራ ጀምራ አንደነበረ መገለጹ ይታወሳል።
ሆኖም ግን በህዳር ወር 2011 ዓ.ም ላይ በኦጋዴን አካባቢ በሙከራ ደረጃ ተጀምሮ የነበረው ድፍድፍ ነዳጅ የማውጣት ስራው መቆሙን የማዕድንና ነዳጅ ሚንስቴር ገልጾ ነበር።
//////////////
የኢታኖል ቤንዚን ድብልቅ አቅርቦትን ማስቀጠል ከየወሩ የነዳጅ ግዥ ግማሽ ሚሊዮን ዶላር ማዳን ያስችላል ተባለ፡፡ ሰፊ ዳሰሳ እናደርግበታለን፡፡
ኢትዮጵያ ከፍተኛ የውጭ ምንዛሪ ከምታወጣባቸው የገቢ ምርቶች ውስጥ ነዳጅ በዋናነት የሚጠቀስ ነው፡፡ ይህንን ከፍተኛ የሆነ ወጪ በተወሰነ ደረጃም ቢሆን ለመቀነስ ይረዳል በሚል ከቤንዚን ጋር በማደባለቅ ለአገልግሎት የሚውል ሥራ አንዱ ነበር፡፡ ዓለም አቀፍ ልምዶችን በመቀመርና ኢትዮጵያ ኢታኖል የማምረት አቅሟን ከግምት በማስገባት ��E5�� ወይም አምስት በመቶ ኢታኖልን 95 በመቶ ቤንዚን በማደባለቅ ለገበያ እንዲቀርብ በተወሰነው መሠረት ለተወሰኑ ዓመታት ሲሠራበት ቆይቷል፡፡
የኢትዮጵያ ነዳጅ አቅራቢ ድርጅት ዋና ሥራ አስፈጻሚ አቶ ታደሰ ኃይለ ማርያም ለሪፖርተር እንደገለጹት፣ ኢታሎኑን ከቤንዚን ጋር በመደባለቅ ለገበያ የማቅረቡ ሥራ ቢገፋ ኖሮ ብዙ ጠቀሜታ ይሰጥ ነበር፡፡ እንደ አገር ከፍተኛ ጠቀሜታ ነበረው፡፡ ሆኖም ከቤንዚን ጋር የሚቀርበውን አምስት በመቶ ኢታኖል ሲያቀርቡ የነበሩ ፊንጫና መተኸራ ፋብሪካዎች በቂ ምርት ማቅረብ ባለመቻላቸው የማደባለቁ ሥራ ሊቋረጥ ችሏል ብለዋል፡፡ በወቅቱ እነዚህ ስኳር ፋብሪካዎች በቀን ያቀርቡት የነበረው ከ50 እስከ 60 ሺሕ ሌትር ኢታኖል ከቤንዚን ጋር ተደባልቆ ለአዲስ አበባና ለአካባቢው ከተሞች ይቀርብ እንደነበር አስታውሰዋል።
በዚህን ያህል መጠን በሱሉልታ ነዳጅ ዲፖ ተደባልቆ የሚቀርበው ምርት ብቻ በወቅቱ በየወሩ ለነዳጅ ግዥ ይወጣ የነበረውን ከግማሽ ሚሊዮን ዶላር ያላነሰ ወጪ ለማዳን በማስቻሉ ጥቅሙን በመረዳት የኢታኖልና ቤንዚን ድብልቅ ምጣኔን ወደ አስር በመቶ ለማሳደግ ጭምር ታቅዶ ተጨማሪ ጥናትና ዝግጅት ተደርጎ እንደነበርም አቶ ታደሰ ያስታውሳሉ፡፡
የኢታኖልን ድብልቅ መጠኑን ወደ አሥር በመቶ ለማሳደግና በአዲስ አበባና በአካባቢው የተወሰነውን ኢታኖል ድብልቅ ቤንዚን ሥርጭት በመላ አገሪቱ ለማዳረስ ታቅዶ እንደነበረ፣ ይህንን ዕቅድ ለማሳካትም በወቅቱ ከነበሩ ስኳር ፋብሪካዎች በተጨማሪ ሌሎች አዳዲስ አሥር ስኳር ፋብሪካዎች እንደሚገቡ ታሳቢ መደረጉን ገልጸዋል፡፡
ነገር ግን ታሳቢ የተደረጉት አዳዲስ ፋብሪካዎች ግንባታ መዘግየት ዕቅዱን ለማሳካት እንዳላስቻለ፣ ይባስ ብሎ ኢታኖልን ያመርቱ የነበሩት ስኳር ፋብሪካዎች የምርት መጠንም በማሽቆልቆሉ ለአዲስ አበባና አካባቢዋ ይቀርብ የነበረው የኢታኖል ድብልቅ ቤንዚን ስርጭት እንዲቋረጥ ማስገደዱን ገልጸዋል፡፡
በነዳጅና በነዳጅ ውጤቶች ሙያ ላይ ለረዥም ዓመታት የሠሩት ሰርካለም ገብረ ክርስቶስ (ዶ/ር)፣ ለሪፖርተር እንደገለጹትም ኢታኖል ድብልቅ ቤንዚን እንደ ኢትዮጵያ ላለ አገር ጠቃሚ ነው፡፡ ይህንን አሰራር ማስፋት ይቻል እንደነበር የገለጹት ባለሙያው ፣ በዚህ መንገድ የቤንዚን ወጪን ከ10 እስከ 15 በመቶ መቀነስ ቢቻል ከወጪ ቅናሹ ይገኝ የነበረው ጥቅም ቀላል የሚባል እንዳልሆነ አስረድተዋል። እንደ ብራዚልና ኩባ ያሉ አገሮች የኢታኖል ድብልቅ ቤንዚንን እስከ 40 በመቶ ወይም E40 ማድረሳቸው የጠቀሜታው ማሳያ መሆኑን የሚያነሱት ሰርካለም (ዶ/ር)፣ እነዚህ አገሮች ቤንዚን ላይ ብቻ ሳይሆን በናፍጣ ላይም እንደሚጠቀሙ አስረድተዋል፡፡ የእነዚህ አገራት ልምድ የሚያሳየው የቤንዚን ወጪያቸውን በከፍተኛ ደረጃ መቀነስ መቻለቸውን እንደሆነ በመጥቀስ ፣ ኢትዮጵያም ኢታኖልን ለማምረት የሚያስችል አቅምም ሆነ ዕድሉ ስላላት ይህንን አሰራር በማስቀጠል ተጠቃሚ መሆን እንዳለባት ይመክራሉ።
ከቅርብ ወራት ወዲህ ዓለም አቀፍ የነዳጅ ዋጋ ከፍ ማለት ኢታኖልን ድብልቅ ቤንዚን የሚጠቀሙ አገሮች ኢታኖል በሰፊው ወደ መጠቀም በመግባት ሸክማቸውን ለማቃለል እየሞከሩ ሲሆን፣ ከሰሞኑ አንዳንድ የአሜሪካ ግዛቶችም የኢታኖልን የድብልቅ መጠንን እስከ 15 በመቶ የማሳደግ ውሳኔ ማሳለፋቸውም በምሳሌነት የሚጠቀስ ነው።
በኢትዮጵያ ኢታኖልን ከቤንዚን በመደባለቅ ይተገበር የነበረው አሠራር ከተቋረጠ ከአራት ዓመታት በላይ እንደሆነው የጠቆሙት አቶ ታደሰ፣ ይህ አሠራር እየጎለበተ መጥቶ ቢሆን ኖሮ፣ በተለይ የነዳጅ ዋጋ በናረበት በአሁኑ ወቅት ኢታኖልን ከቤንዚን መደባለቅ የቤንዚን የችርቻሮ ዋጋን በመቀነስ ለመንግስትም ሆነ ለማሕበረሰቡ ከፍተኛ አስተዋጽኦ ያበረክት ነበር ብለዋል፡፡ የኢታኖልና ቤንዚን ድብልቅ ለገበያ ይቀርብ በነበረበት ወቅት ይኸው የዋጋ ቅናሽ በግልጽ ተስተውሎ ነበር፡፡ የአንድ ሌትር ቤንዚን ዋጋ 21 ብር 87 ሳንቲም ይሸጥ በነበረበት ወቅት ኢታኖል ድብልቅ 21 ብር ከ33 ሳንቲም ይሸጥ እንደነበርና በሁለቱ መካከል በአማካይ 55 ሳንቲም ልዩነት እንደነበረ መረጃዎች ይጠቁማሉ
ይህ ልዩነት ቀላል የማይባል መሆኑን የሚጠቅሱት አቶ ታደሰ፣ አገልግሎቱ ባይቋረጥና የሚደባለቀውን የኢታኖል መጠን እየጨመሩ መሄድ ቢቻል እንደ አገር ትልቅ ጠቀሜታ ያስገኝ ነበር ይላሉ፡፡ ሰርካለም (ዶ/ር) ም በዚህ ሐሳብ ይስማማሉ፡፡ አብዛኛው የቤንዘን ተሽከርካሪ አዲስ አበባ ላይ በመሆኑ ከ70 እና 75 በመቶ በላይ የኢትዮጵያ ቤንዚን ፍጆታ በአዲስ አበባና በዙሪያዋ እንደሚቀርብ የገለጹት ሰርካለም (ዶ/ር)፣ በዚህም ምክንያት የኢታኖል ድብልቅ ቤንዚን አዲስ አበባ ላይ እንዲተገበር መደረጉ ተገቢ እንደነበር ገልጸዋል። ነገር ግን በአምስት በመቶ የተጀመረው ሥራ ወደ 10 በመቶ ያድጋል ተብሎ ሲጠበቅ መቋረጡ ትክክል እንዳልሆነ ያስረዳሉ። ይህም በአግባቡ አቅዶ መተግበር ላይ አገራዊ ችግር ያሳያል ይላሉ፡፡ ኢታኖል ከቤንዚን ደባልቆ መጠቀም ጠቀሜታው ታውቆ ሥራው ከተጀመረ በኋላ መቋረጡም የመንግሥትን ትከሩት ማጣት ያመለክታል ብለዋል፡፡ ከዚህ በፊት ለኢታኖልን ድብልቅ ተብሎ የተቋቋመው መሥሪያ ቤት ዛሬ የት እንዳለ አይታወቅም የሚሉት ሰርካለም (ዶ/ር)፣ በተጠና መልኩ ሥራው ቀጥሎ ቢሆን ኖሮ ጠቀሜታው ለአገር ነበር ሲሉ ቁጭታቸውን አካፍለዋል።
አሁንም ይህንን አገልግሎት መልሶ መጀመር ብዙ ጠቀሜታ እንደሚኖረው የጠቀሱት አቶ ታደሰ በበኩላቸው፣ አዳዲስ የስኳር ፋብሪካዎች ኢታኖልን በብዛት የሚያመርቱ ከሆነ አሁንም ኢታኖል ድብልቅ ቤንዚንን መልሶ ለገበያ ማቅረብ የሚቻልበት ትልቅ ዕድል መኖሩን ጠቁመዋል።
ከቤንዚን ጋር የሚደባለቀውን ኢታኖል የሚያመርቱት የአገሪቱ ስኳር ፋብሪካዎች አሁንም ኢታኖል እያመረቱ ቢሆንም፣ የሚያመርቱት የኢታኖል መጠን ግን በሚፈለገው ልክ ባለመሆኑ ምርቱ በአሁኑ ወቅት ለአክኮልና እንደ “ሳኒታይዘር” ላሉ የንጽህና መጠበቂያ ምርቶች ግብዓትነት ብቻ እየዋለ ነው።
በተለይ ከኮቪድ-19 ወረርሽኝ መከሰት በኋላ በየፋብሪካዎቹ የሚመረተው ኢታኖል የንጽህና መጠበቂያ ምርቶችን ለማምረት በግብዓትነት እንዲውል በመደረጉ ለቤንዚን የሚሆን ኢታኖል ማቅረብ እንዳይታሰብ ማድረጉ ይነገራል፡፡ በሌላ በኩል ኢታኖል ረዥም ጊዜ መጠቀም ተሽከርካሪ ላይ ችግር አለው የሚል አስተያየት የሚሰነዘር ቢሆንም፣ ሰርካም (ዶ/ር) ግን ያን ያህል ችግር እንደሌለው ጠቁመዋል፡፡ ስለዚህ ጠቀሜታው የጎላ ስለሆነ አሁንም ለመሥራት ጊዜው አልረፈደም ሲሉ መክረዋል፡፡
////////////
የብረትና የሲሚንቶ ምርቶች ከፍ ላለ የገበያ ውስጥ ህገወጥ ድርጊት መጋለጣቸው የኮንስትራክሽን ላይ የተሰማሩ ድርጅቶችን ከጨዋታ ውጪ አድርጓቸዋል ተባለ፡፡ የአንድ ኩንታል ሲሚንቶ ዋጋ በአሁኑ ወቅት 1800 ብር ደርሷል፡፡ በተመሳሳይ ከዓመታት በፊት በ25 ብር ይሸጥ የነበረ ብረት አሁን ላይ ዋጋው 122 ብር መድረሱ ከቁጥጥር ውጪ የወጣው ህገወጥ ገበያ ማሳያ ሆኖ ተጠቅሷል፡፡ ርዕሰ ጉዳዩን በስፋት እንቃኘዋለን፡፡
የዋጋ ንረት በከፍተኛ ሁኔታ ተፅዕኖ እያሳደረባቸው ከሚገኙ የኢኮኖሚ ዘርፎች ውስጥ የኮንስትራክሽን ኢንዱስትሪው ተጠቃሽ ነው፡፡ ኢንዱስትሪው ለአገራዊ ኢኮኖሚው አስተዋጽኦ ያለው ድርሻ ከፍተኛ የሚባል የነበረ ሲሆን በአሁኑ ወቅት ግን ከዋጋ ንረት ጋር በተያያዘ ከፍተኛ ችግር ውስጥ መዘፈቁ እየተነገረ ነው፡፡
ቀድሞም ቢሆን ብልሹ አሠራሮች የነበሩበት ይህ ዘርፍ ለተከታታይ ዓመታት በኮንስትራክሽን ግብዓቶች ላይ ፍጹም ተጠባቂ ባልሆነ ሁኔታ የታየው የግብዓቶች የዋጋ ጭማሪ ኢንዱስትሪውን በእጅጉ ስለመጉዳቱ የኢትዮጵያ ኮንትራክተሮች ማኅበር በተደጋጋሚ ሲገልጽ ቆይቷል፡፡
የማኅበሩ ፕሬዚዳንት አቶ ግርማ ሃብተማርያም (ኢንጂነር) እንደገሉጸትም በተለይ ባለፉት ሁለት ሦስት ዓመታት በግንባታ ግብዓቶች ላይ እየታየ ያለው የዋጋ ጭማሪ ብዙ ፕሮጀክቶች እንዲቋረጡ ምክንያት ከመሆኑም በላይ ብዙ ኮንትራክተሮችንም ለኪሳራ የዳረገ እስከመሆን ደርሷል፡፡ ችግሩ በዚህ ብቻ የማይገለጽ መሆኑን የጠቆሙት ፕሬዚዳንቱ በግንባታ ዕቃዎች መወደድ ሳቢያ የኮንስትራክሽን ድርጅቶች ብዙ ሠራተኞችን ለመቀነስ መገደዳቸውንም ይጠቁማሉ፡፡
ኪሳራ ውስጥ ላለመግባት የዋጋ ጭማሪውን ተቋቁመው በእጅ ያሉ ሥራዎቻቸውን ለማጠናቀቅ የሚተጉትም ቢሆኑ ዕድለኛ ሆነው ሥራቸውን ካጠናቀቁ በኋላ ቀጣይ ህልውናቸው ምን ሊሆን እንደሚችል እንኳን ለመገመት ያዳግታል ይላሉ፡፡ በሁሉም የግንባታ ዕቃዎች ላይ ዋጋ ጭማሪው ተገማች ያልሆነ መሆኑን የሚጠቅሱት አቶ ግርማ በተለይ ብረትና ሲሚንቶ ዋጋውም ሆነ አጠቃላይ የግብይት ሒደቱ የተበላሸ ሆኖ መቀጠሉ ለዚህም ሁነኛ መፍትሔ ሊበጅ አለመቻሉ ችግሩን የበለጠ እንዳባባሰው አመልክተዋል፡፡
ማኅበራቸው ከተቋቋመ ጊዜ ጀምሮ ከዋጋና ከግብይት ጋር የተያያዙ ችግሮች እንዲፈቱ ለመንግሥት አቤቱታ የቀረበ ቢሆንም መፍትሔ የተባሉ ውሳኔዎች በተግባር ሊቀየሩ ባለመቻላቸው በተለይ የብረትና የሲሚንቶ የግብይት ሥርዓት ብልሽት ከድጡ ወደ ማጡ እየሆነ መሄዱንም በምሬት ገልጸዋል፡፡
ሌላው ቀርቶ በቅርቡ በተከታታይ የሲሚንቶ ጉዳይ መፍትሔ ተበጅቶለታል፣ የተለያዩ ዕርምጃዎች ተወስደዋል እየተባለ እንኳን የታየ ለውጥ አለመታየቱን ፤ ይባስ ብሎ አሁን ላይ የአንድ ኩንታል ሲሚንቶ ዋጋ 1,800 ብር መድረሱን በምሳሌት ጠቅሰዋል፡፡
አሁን ደግሞ በብረት ገበያ ውስጥ ተመሳሳይ ችግር እየታየ ስለመሆኑ የሚጠቁሙት ኮንትራክተሮች የዋጋ ጭማሪው ብቻ ሳይሆን አጠቃላይ የብረት ግብይት ሕገወጥ አሠራሮች እየታዩበት መሆኑን ይገልጻሉ። የብረት ዋጋው ዓለም አቀፍ ገበያን ያላገናዘበ እየሆነ መምጣቱንም ያስረዳሉ፡፡ እንደ አቶ ግርማ ገለጻ ከሆነ ደግሞ ከአራትና አምስት ዓመት በፊት የገባ ብረት ሳይቀር ተሸሽጎ ቆይቶ አሁን በተጋነነ ዋጋ በመሸጥ ላይ ነው።
አምስትና ስድስት ዓመት አንድ ኪሎ አርማታ ብረት ከ20 እስከ 25 ብር ያስገቡ ሰዎች አሁን 122 ብር እየሸጡ ነው መባሉንም ይጠቅሳሉ፡፡
��በአጠቃላይ የዚህን አገር ገበያ አለመጠየቅ ይሻላል፤�� የሚሉት አቶ ግርማ በገበያው ብዙ ነገር እየተበላሸ በመሆኑ ኢንዲስትራውን እየጎዳና ሠራተኞችንም እየተፈናቀለ እንደሚገኝ በመጥቀስ አፋጣኝ መፍትሔ ይበጅለት ይላሉ፡፡ በዋግ ጭማሪና በተወነባበደው የገበያ ሥርዓት ብቻ ከደረጃ አንድ ኮንትራክተሮች ውስጥ ጥቂት የማይባሉ ሥራ አጥተው አራትና አምስት ዓመት እንዳለፋቸው ፣ አንዳንዶቹ ደግሞ ለባለሙያዎች ክፍያ እየከፈሉ የተቀመጡ ቢሆንም አዳዲስ ፕሮጀክቶችን ማግኘት አለመቻላቸውን ጠቅሰዋል፡፡
የኮንስትራክሽን ሥራ ተቀዛቅዟል እየተባለ በሌላ በኩል ደግሞ የግንባታ ግብዓቶች ዋጋ እያሻቀበ መምጣት ብዙዎችን እያነጋገረ ሲሆን፣ በተለይ የብረትና የሲሚንቶ ዋጋ ፈጽሞ አልቀመስ ያለበት ምክንያት ግንባታዎች በዝተው ሳይሆን የግብይት ግብዓቶች መበላሸት ያመጣው ችግር መሆኑን ይገልጻሉ፡፡ የአገር ውስጥ ብረት አምራቾች ግብዓት የሚሆናቸውን ጥሬ ዕቃ ከውጭ የሚያስመጡ ቢሆንም በትክክል ወጪያቸውን አስልተው ትክክለኛ የትርፍ ህዳግ ይዘው እየሸጡ ነው ብሎ ለማመን እንደሚከብድ አቶ ግርማ ገልጸዋል፡፡ ነገር ግን ከውጪ የሚመጣው የጥሬ ዕቃው ቀረጥ ይታወቃል ማምረቻ ወጪያቸውና የሚሸጥበትን ዋጋ በአማካይ መገመት ቢቻልም የተጋነነ ትርፍ ተይዞ ሲሸጥ መንግሥት ቁጥጥር አለማድረጉ ትልቅ ችግር እየፈጠረ እንደሆነ ይገልጻሉ።
ስለዚህ አጠቃላይ የማምረቻ ዋጋው እየታወቀ ከውጭ የሚገባውም ከማንም የተሸሸገ ሳይሆንም መንግሥት ገበያውን ለማረጋጋት የሚያስችል ዕርምጃ ባለመወሰዱ ችግሩ መባባሱንም ያመለክታሉ፡፡ ዋጋን ለመቆጣጠር የተቋቋሙ እንዲሁም የሙስና ኮሚሽን አሉ ቢባልም እነዚህ ተቋማት ኃላፊነታቸውን በአግባቡ ባለመወጣታቸው ለችግሩ መባባስ ተጠቃሽ ያደርጋሉ፡፡
��በቀደመው ጊዜ አንድ ቤተሰብ ነበር ብረት የሚያስመጣው�� ያሉት አቶ ግርማ አንድ ሰሞን ደግሞ ደረሰኝ አትጠይቁን የግንባታ ቦታ (ሳይት) ድረስ በቅናሽ እናመጣለን የሚሉ ሁሉ መምጣታቸውን በመጥቀስ የችግሩን ደረጃ ያሳያሉ፡፡
አንድ የደረጃ አንድ ኮንትራክተር ደግሞ በዓለም አቀፍ ደረጃ የብረት ዋጋ የቀነሰ ቢሆንም ኢትዮጵያ ውስጥ እየተሸጠበት ያለው ዋጋ አሁንም ሊቀንስ አለመቻሉና በሕገወጥ መንገድ የሚገቡ የብረት ምርቶች ገበያ ውስጥ ችግር እየፈጠሩ መሆኑን ጠቅሰዋል፡፡
///////////
ከፍተኛ ኪሳራ ላይ የሚገኘው የኬንያ አየር መንገድ ለኢትዮጵያ መንግሥት የክፍያ ጥያቄን አቀረበ።
ክፍያው የኬንያ አየር መንገድ በኢትዮጵያ ለሰጣቸው አገልግሎትና ሽያጮች ገንዘብ ከብር ወደ ዶላር ተቀይሮ መሰጠት የነበረበት እንደሆነ አስረድቷል፡፡
አየር መንገዱ ተመሳሳይ ጥያቄን ለናይጄሪያ መንግሥትም አቅርቧል።
በአሠራር ደረጃ አየር መንገዶች አገልግሎታቸውን በውጭ አገራት ሲሸጡ በአገሬው ገንዘብ ከተገበያዩ በኋላ ገንዘባቸው የሚሰጣቸው በዶላር ነው።
የኬንያ አየር መንገድ በሁለቱ አገራት የሚገኘውን ገንዘቡን ማግኘት ያልቻለው በውጭ ምንዛሬ እጥረት እንደሆነ ይታመናል።
የኬንያ ባለሥልጣናት ለኬንያ አየር መንገድ የሚገባውን ክፍያ እንዲፈፅሙ የኢትዯጵያንና የናይጄሪያን ባለሥልጣናት በማነጋገር ላይ እንደሆኑ ተዘግቧል።
ገንዘቡ በአየር መንገዶችና በአገሮች መካከል የገቢ ክፍያ ልውውጥ በጊዜ ባለመካሄዱ የተከሰተ ችግር መሆኑ ታውቋል።
የኬንያ አየር መንገድ ሁለቱ መንግሥታት ሊከፍሉት ይገባ የነበረ በሚሊዮን ዶላር የሚቆጠር ገንዘብ ሊያገኝ ያልቻለው ግን በዋናነት በውጭ ምንዛሬ እጥረት ምክንያት ነው።
የኬንያ አየር መንገድ በአውሮፕላን ነዳጅ ዋጋ ማሻቀብ የተነሳ፣ እንዲሁም በሌጎስና አዲስ አበባ ባጋጠመ የውጭ ምንዛሬ እጦት ገንዘቡ ስላልተከፈለው ባለፉት ስድስት ወራት ብቻ 82 ሚሊዮን ዶላር ከስሬያለሁ ብሏል።
ሆኖም የኬንያ ባለሥልጣናት አየር መንገዱ ከሁለቱ አገሮች ምን ያህል ገንዘብ ማስመለስ እንዳልቻለ ትክክለኛ አሐዝ ከመግለጽ ተቆጥበዋል።
የአገሪቱ ባለሥልጣናት አሁን ይህን ለኬንያ አየር መንገድ የሚገባውን ገንዘብ ከአዲስ አበባና ከሌጎስ ለማግኘት ዲፕሎማሲን አማራጭ አድርገዋል።
በተያያዘ ዜና የዓለም አቀፉ አየር ትራንስፖርት ማኅበር ይፋ እንዳደረገው ለተለያዩ አየር መንገዶች መከፈል የነበረበት ግማሽ ቢሊዮን ዶላር የሚጠጋ ገንዘብ በናይጄሪያ ቀርቷል።
የዱባዩ ኢምሬትስ ግሩፕ በተመሳሳይ በናይጄሪያ የሚገኘው ገንዘቤን ማግኘት አልቻልኩም በሚል ወደዚያ የሚያደርጋቸውን በረራዎች ማቋረጡ ይታወሳል።
ይህም የዶላር እጥረት በአቪየሽን ኢንዱስትሪው የፈጠረው ሌላ ችግር ሆኖ ተመዝግቧል።
የውጭ አየር መንገዶች አገልግሎታቸውን መሸጥ ያለባቸው በአገሬው የመገበያያ ገንዘብ ነው።
ይሁንና ገንዘባቸውን የሚወስዱት ግን ወደ አሜሪካን ዶላር ከተቀየረ በኋላ ነው።
መደበኛ አሠራሩ ይህ ይሁን እንጂ በርካታ አገሮች በውጭ ምንዛሬ እጥረት በመቸገራቸው ዕዳቸውን በዶላር ለመክፈል እየተንገታጉ ይገኛሉ።
በአፍሪካ የሕዝብ ቁጥር ቀዳሚ የሆነችው ናይጄሪያ ከቅርብ ጊዜ ወዲህ በገጠማት የውጭ ምንዛሬ እጥረት ግዙፍ የውጭ ኩባንያዎች ላቀረቡት ምርትና አገልግሎት በሚከፈላቸው ዶላር መጠን ላይ ገደብ ለመጣል ተገዳለች።ሲል የዘገበው ቢቢሲ ነው፡፡
////////////////////
አነስተኛው ኢሲያዊት አገር የዘይት ሚንስትር ሾመች፡፡ አገሪቱ በተመሳሳይ የቡና ሚንስትር መሾሟም ዓለምን ጉድ አሰኝቷል፡፡ ዝርዝር አለን፡፡
ዘጠኝ ሚሊዮን ገደማ ህዝብ ብዛት ያላት እስያዊቷ ሀገር ፓፑዋ ኒው ጊኒ የዘይት ሚኒስቴር ያቋቋመች ሲሆን ጉዳዩ የብዙዎችን ትኩረት ስቧል።
ከአንድ ወር በፊት በድጋሚ የሀገሪቱ ጠቅላይ ሚንስትር ሆነው የተመረጡት ጄምስ ማራቢ አዲሱን ካቢኔያቸውን አዋቅረዋል።
ጠቅላይ ሚኒስትሩ 33 አባላት ባለው በአዲሱ ካቢኔያቸው የዘይት ሚኒስትር የሾሙ ሲሆን ሀገሪቱ ወደ ውጪ የምትልካቸውን መሰረታዊ የግብርና ምርቶች ለማሳደግ ማቀዷ ለአዲሱ ሚንስቴር መቋቋም ዋነኛ ምክንያት እንደሆነ ገልጸዋል።
ፓፑዋ ኒው ጊኒ የግብርና ምርቶችን ወደ ውጭ ሀገራት በመላክ የምትታወቅ ሲሆን ከዚህ ውስጥ የዘይት ምርቶች 40 በመቶ ድርሻ ሲኖራቸው ቡና ደግሞ የ27 በመቶ ድርሻ አለው።
ወደ ውጪ ሀገራት የሚላከውን የዘይት ምርት ለማሳደግ ሲባልም ሚንስቴር ተቋም ለማቋቋም መወሰኗን ጠቅላይ ሚንስትር ማራፒ ተናግረዋል።
ጠቅላይ ሚኒስትሩ በአዲሱ ካቢኔያቸው ከዘይት ሚንስትር በተጨማሪ የቡና ሚንስትር የሾሙ ሲሆን የተቋሙን ዋና መቀመጫ ከዋና ከተማው ወደ ገጠር አዛውረዋል።
ጆ ኮሊ የፓፑዋ ኒው ጊኒ የቡና ሚንስትር ተደርገው የተሾሙ ሲሆን የሚንስቴሩ ዋና መቀመጫ ጽህፈት ቤት ቡና በብዛት ወደሚመረትበት ደቡባዊ የሀገሪቱ ክፍል ይሆናል ተብሏል።
////////////////////
ዐውደ ቢዝነስ የዕለቱ ዘገባችን ተጠናቀቀ፡፡ አብራችሁን ስለቆያችሁ በድጋሚ ልባዊ አክብሮትና ምስጋናችን ይድረሳችሁ፡፡ መሰናዷችን ዳግመኛ በአዳዲስ፤ ትኩስና ጠቃሚ የቢዝነስ፣ የፋይናንስና ኢኮኖሚ መረጃዎች ስትመለስ ደግመን እንደምናገኛችግሁም ተስፋችን ብሩህ ነው፡፡ እስከዛው በያላችሁበት በሰላምና ጤና ቆዩን፡፡